የሥራ ውሎች፤ የሠራተኛ ሥራ እንዳይሠራ መከልከልና ለተወሰነ ጊዜ የማገልገል ወይም ካሣ የመክፈል ግዴታ፡፡


ሀ- እንደመግቢያ
በመጀመሪያ የሥራ ዉሎችን የሚገዙ ስንት ሕጎች  እንዳሉ መግለጽ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ሁለት ናቸዉ፡፡ እነሱም፡-
1-             በአዋጅ ቁጥር 377/1996 ሥር የሚተዳደሩ የሥራ ዉሎች፡፡ ይህ ሕግ በአሠሪና የሥራ አመራር (ማኔጅመንት) ኣባል ያልሆኑ ሠራተኞች ግንኙነታቸዉን የሚገዙበት ሕግ ነዉ፡፡ እዚህ ላይ ሁለት መሠረታዊ የሆኑ ነገር ግን ብዙ ጊዜ በአግባቡ ልብ የማይባሉ ነጥቦችን ጠቅሼ ልለፍ፡፡ አንደኛዉ  አሠሪዉና የሥራ አመራር (ማኔጅመንት) አባል የሆኑ ሠራተኞች ግንኙነታቸዉን በዚህ አዋጅ አማካኝነት  ለመግዛት ከፈለጉ  በስምምነታቸዉ መሰረት ይህንን ማድረግ ይችላሉ፡፡ በሥራዉ ዓለም ግን ይህ ሲደረግ አይታይም፡፡ ምክንያቱን የሚያዉቀዉ እግዛብሔር ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሁለተኛ፡፡ የሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የአሠሪና ሠረተኛ ዋና ዋና ግዴታዎች ምን እንደሆኑ የሚዘረዝር ቢሆንም ፤ ሌሎች ተጨማሪ ግዴታዎች ግን በተጨማሪ ዉሎችም ሆነ በተጨማሪ ይዘቶች ተዋዋይ ወገኖች  እንዳይገቡ አይከለክልም፡፡
2-            በ1960 ዓ.ም. በወጣዉ የፍትሓብሔር ሕግ መሠረት የሚተዳደሩ የሥራ ዉሎች፡፡ ይህ ሕግ ተፈጻሚነቱ አሠሪና የሥራ መሪ (ማኔጅመንት) አባል  በሚገቡት የሥራ ዉል ላይ ነዉ፡፡ ከላይ እንደተመለከተዉ አሠሪና ሠራተኛዉ ይህ የፍትሓብሔር ሕግ ተፈጻሚ እንዳይሆንባቸዉና በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሠረት ግንኙነታቸዉ እንዲገዛ ለመምረጥ ይችላሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጸዉ የተለመደ አሰራር ግን አይደለም፡፡ ጠበቆች የደንበኞቻቸዉ መብት የበለጠ የሚጠበቅበትን ሁኔታ ቀድሞ በማየት ትክክለኛዉን አግባብ ሊያመላክቱ ይገባል፡፡
ለ- እያየን እንዳላየን...
ሌሎች  በጣም አስፈላጊ ሁነዉ እያለ የተዘነጉ ሁለት ዓበይት የሕግ ነጥቦችን ደግሞ ልጨምር፡፡ የመጀመሪያዉ ሠራተኛዉ ከአሠሪዉ ጋር ወደፊት እንዳይወዳደር ለማድረግ የፍትሓብሔር ሕጉ በግልጽ እዉቅና ሰጥቶና መሠረቶቹንም አስቀምጦ  እያለ አሰራሩ ግን ፍጹም ሊባል በሚችል ሁኔታ ጥቅም ላይ ሲዉል አይታም፡፡ በርግጥ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ይህንን መሰሉን ሁኔታ ሳይፈቅድም ሳይከለክልም ጉዳዩን በዝምታ አልፎታል፡፡ ሆነም ግን የአሠራሩን መፈቅድና መከልከል ለማወቅ  አንድ ነገር ብቻ ማየት ይበቃል፡፡ በሕግ መርህ መሠረት ያልተከለከለ ነገር ሁሉ የተፈቀደ  ነዉ፡፡ እዚህም ላይ ጠበቆች የደንበኞቻቸዉን ጥቅም በሚያራምድ መልኩ ሊመክሩ ይገባል፡፡  ሁለተኛዉ አንድን ሰዉ አሰልጥኖ በመቅጠር ለተወሰነ ጊዜ አሠሪዉን እንዲያገለግል የሚገደድበት የስምምነት ዉል አግባብ ነዉ፡፡ ይሄ በሁሉም ሕጎች በግልጽ ተደንግጎ እያለ የሚጠቀምበት ሰዉ ግን ያለም አይመስልም፡፡ ምክንያቱ አለማወቅ ይሁን  አለመፈለግ አሁንም  ግልጽ አይደለም፡፡ ምንአልባት ጥያቄዉ በራሱ መልሱን ይናገራል ካልተባለ በቀር፤ አንድ ነጥብ ላንሣ፡፡ ለመሆኑ አንድ አሠሪ ሠራተኘዉ ወደፊት በጥራትና በብቃት እንደሚያገለግለዉ እርግጠኛ ካልሆነ በቀር ምን ቢሆነኝ ብሎ  በራሱ ኪሣራ "ብቁ" ያልሆነን ሠራተኛ ቀጥሮ ያሰራዋል? ለምንስ ብሎ ያሰለጥነዋል? የዚህ ጥያቄ ትክክለኛ  መልስ  የአሰራሩ ሕጋዊነትና ሕገወጥነት የሚወድቀዉ በአሰሪዉና ሠራተኛዉ ስምምነት አረቃቀቅ እንጂ በሕጎቹ ክልከላ ላይ ስላለመሆኑ ግልጽ ያደርገዋል፡፡  
ሐ - የታተሙ የሠበር ችሎት ዉሣኔዎች በሠራተኛ ትምሕርትና ሥልጠና ጉዳዮች ላይ፡፡
ደግነቱ የሠበር ችሎት ተመሣሣይ በሆኑ ጉዳዮች ከላይ የተመለከቱት ግንዛቤዎች ሕጋዊ ስለመሆናቸዉ ተደጋጋሚ አስገዳጅ ዉሣኔዎችን ሰቷል፡፡ ለዓብነት ያሕል እነዚህ የታተሙትን ከዚህ በታች ገልጫለሁ፡፡
1-   በአመልካች / ሃርሴማ ሰለሞን እና መልስ ሰጪ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (የ//. 33473፤ ቅጽ 8)፤ ገጽ 322፡፡
2-   በአመልካች የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንቲትዩት እና ተጠሪ አቶ ተፈሪ ማሞ (የ// 49453፤ ቅጽ 9)፤ ገጽ 192፡፡
3-  (አመልካች ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ተጠሪዎች እነ ዮናስ ካሳ (ሁለት ሰዎች)፤ (የሠ// 46574፤ ቅጽ 12)፤ ገጽ 90፡፡